Skip to content

ኢትዮጵያ – እግዜር – ረኃብ

December 17, 2013

ረኃብ ካለ ርኁብ አለ! የኪዳነ ወልድ ክፍሌው ‹መፅሃፈ ሰዋሰው ወግስ፤ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ› ደግሞ ረኃብን ‹የምግብ እጦት፤ ቀጦና፤ ችጋር› ብሎ ሲፈታው፤ ‹ርኁብ›ን ደግሞ ፡ ‹የተራበ የተቸገረ፤ ራብተኛ፤ ራብ የያዘው ምግብ ያረገዘው› በማለት ይተረጉመዋል፡፡ በርግጥ በዚህ ፍች ረኃብ (Hunger) እና ችጋር (Famine) አንድ ላይ ተደባልቀው ተቀምጠዋል፤ አንድ ባይሆኑም፡፡

በዚህች አጭር ጦማር ‹ራብ የያዘው ምግብ ያረገዘው› ኢትዮጵያዊ በረኃብ ጊዜ ከጭንቀቱ እና ግራ ከመጋባቱ ብዛት በዙሪያው ያሉ ነገሮችን ሁለ ጨርሶ ይጠብቀኛል ይወደኛል ብሎ ለሚያስበው ፈጣሪ ያቀረበውን ልመና / ቁጣና ስድብ / ትችት ለማየት ነው የታሰበው፡፡ ከዛ በተረፈ ኢትዮጵያና ረኃብ፤ የረኃብ ፖለቲካ፣ የረኃብ መነሻና መድረሻ የሚሉ ሀሳቦችን ብዙ ፀሃፊዎች በየጊዜው የዳሰሷቸው ጉዳዮች እንደመሆናቸው የዚህ ጦማር አካል አልሆኑም፡፡

ሰው በረኃብ ወቅት የልቡን አውጥቶ መናገሩ እውነት ነው፡፡ ስለእንጀራ ሲል ሰው ብዙ ነገር ያልፋል፡፡ እንዲህ እስኪባል፡

‹‹እዛ ወንዝ ማዶ፣ እንጀራ አለ ብለው አይነግሩም ለድሃ፤

በቀን በሌት ብሎ፣ አቆራርጦት ያድራል አርባራቱን ውሃ፡፡››

ሰው በመከራ ጊዜ አጋዤ ይሆናል ብሎ ከጎኑ ይዞት የሚኖረውን አምላክ ‹ወዲያ በል› እስከ ማለት ይደርሳል፡፡ አይሆዶች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የደረሰባቸውን ጭፍጨፋ ከአምላካቸው ብዙ ቢያራርቃቸው፤ አንድ ያልታወቀ አይሁድ በMauthausen Concentration Camp ግድግዳ ላይ እንዲህ አለ፡

If there is a God, He will have to beg my forgiveness

የ1994ቱ (እ.ኤ.አ) የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል ብዙ ሩዋንዳዊያንን አለ የሚሉትን አምላካቸውን ጥርጣሬ ውስጥ እንደከተተው የቅርብ መረጃዎች ያሳዩናል፡፡

ኢትዮጵያዊያንስ? በኢትዮጵያ ታሪክ ከተስፋ አስቆራጭ ጊዜያት ዋነኛው የረኃብ ጊዜ ነው፡፡ ከተስፋ መቁረጡ የተነሳ ኢትዮጵያዊያን በረኃብ ጊዜ በአምላካቸው ላይ ማመፃቸው አልቀረም፡፡ እኔም በረኃብ ወቅት ኢትዮጵያዊያን ‹ይጠብቀናል› ለሚሉት አምላካቸው ከልመና እሰከ ቁጣ የገለፁባቸውን ስንኞች አሰባሰብኳቸው፡፡

ልመና

‹‹እባክህ አምላኬ፤ አዝመራውን ባርከው፣
ሆዴ ሊቀደድ ነው፤ እየራበኝ ሳከው፡፡››

***

‹‹ውሃ እንደተጠማኹ፣ እንጀራ እንደራበኝ፤
ጭራሹን ሳላየው፣ እግዜር ባልገደለኝ፡፡››

***

‹‹እባክህ አምላኬ፤ ነፋሱን መልሰው፤
ወንድም ወንድሙን ፤ ሸጦ ሳይጨርሰው፡፡››

***

‹‹እግዜር ባንድ ነገር፣ አይጠረጠረም፤
 ድሀ ድሀው ሞቶ፣ ባለጠጋ አይቀርም፡፡››

***

‹‹አሻቅቤ ባየው፤ ሰማዩ ቀለለኝ፣
አንተንም ሰፈራ፤ ወሰዱህ መሰለኝ፡፡››

***

‹‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ምግብ ትዘረጋለች!››

‹‹ትችለናለህ ወይ፣ እግዜር በትግያ፤
ከብቱን ብትገልብን፣ ጠመድን ባህያ፡፡››

***

‹‹የእኛ እግዜር ምቶ፣ የእነሱ ቆመና፤
ውሻ ‹ቻዝ› እያሉ፤ አሽበላለጡብን አንኮላና ቁና፡፡››

***

‹‹ግራዝማች ደንጎሎ፣ ፊታውራሪ ጎመን እግዜርን አከሉ፤
 አፍንጫን አቃንተው፣ መልክ አስተካከሉ፡፡››

***

‹‹ከኢትዮጵያ ጸሎት፤ ጣሊያኖች በለጡ፣
በአርባ ዘመናቸው፤ ክንፍ አውጥተው መጡ፣
ፈጣሪ ተጠንቀቅ፤ ወዳንተም እንዳይመጡ፡፡››

***

እግዜርን ግሳፄ

‹‹እግዜር ምድር ወርዶ፣ ጉዱን ነግሬው፤
የደላኝ መስሎታል፣ ተመስገን ብለው፡፡››

***

‹‹ዝናቡ የልህ የልህ፤
 ጠሀዩ የልህ የልህ፤
 እባክህ አምላኬ፣ እንዴት ልሁንልህ፤
 ትዘራው እንደሆን፣ ቅብቅቡ ያውልህ፡፡››

***

‹‹እዚያ ላይ ተቀምጠህ፤ ስታላግጥ በሰው፣
እናትህ ነደደች፤ ሀዘንን ቅመሰው!››

***

‹‹ውጭ ሀገር ይመኛል፣ ዋ ሀበሻ ሞኙ፤
እዚያ እግዜር የለም ወይ፣ እዚህ የሚያውቀኙ፡፡››

***

‹‹ተጣልቻለሁ ካምላክ ጋራ፣ በሌላም አይደል ባንድ እንጀራ፤
 ከለከልከኝ ምነው፣ ሆድ የለህ አትበላው::››

***

‹‹እግዜር እታች ወርዶ፣ እኔ ላይ ወትቼ ስፍራ ብቀይረው፣
ያውቃታል ስራውን፣ ቅዱስ ሚካኤልን ሰውም አላረገው::››

***

‹‹ምን ገደለው – ውጋት፤
ምን ገደለው – ቁርጠት፤
እግዜር ምን ቸገረው፣ አይማኸኝበት፡፡››

***

‹‹ዘጠኝ ታድናለህ፣ አንድ ትገድላለህ፤
የሴት ልጅ ነህና፣ ምን ፍርድ ታውቃለኸ፡፡››

***

‹‹ከሰራኸው ስራ፣ ሁሉም ተበላልህ፤
 እሬት በመምረሩ፣ ድንጋይ በጥጣሬው ሁለቱ ቀረልህ፡፡››

***

‹‹እግዜርም እንደሰው፤ በሀሰት እየማለ፣
አንድ እንጀራ ብለው፤ ሙት የለኝም አለ፡፡››

***

‹‹እፋረደዋለሁ፣ አልለቀው በዋዛ
ከምድር ላይ ሲያጠፋ፣ የሰውን ልጅ ለዛ፡፡››

***

‹‹የኔ መሪጌታ፤ እርስዎማ ምን ይሉ፣
የኔ መሪጌታ ፤ እርስዎ ምን ይበሉ፣
እሱ እየገደል፤ ተዝካሩን ሲበሉ፡፡››

***

ምንጭ:

ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ: ‹ሰሚ ያጡ ድምፆች› ፣ ቦጋለ ተፈሪ: ‹ትንቢተ ሼህ ሑሴን ጅብሪል› ፣ የሕዝብ

From → Uncategorized

One Comment
  1. “ሰው በመከራ ጊዜ አጋዤ ይሆናል ብሎ ከጎኑ ይዞት የሚኖረውን አምላክ ‹ወዲያ በል› እስከ ማለት ይደርሳል።”

    በሌላው ይኾን ይኾናል። በኢትዮጵያ ግን እንዲኽ አይደለም። ሐቁን እንነጋገር ካልን፤ በኢትዮጵያ እግዜርን ያለው “ረኀብ የያዘው ምግብ ያረገዘው ” ሳይኾን “አገራዊ መሠረት የለሽ አይዲዮሎጂ የያዘው፥ አገራዊ ዕውቀት ያረዘው [የዐረዘው = ያነሰው፥ የጎደለው፥ ያጸጸው፥ ያለቀበት የሣሣበት] ጥጋበኛ ትውልድ ነው።

    በዚኽ ጕዳይ መከራከር ይቻላል። ጥቂት ቅር ያለኝ ግን፤አንዳንድ አባባሎች አለቦታቸው መግባታቸው። ያውም ቅኔኣዊ ለዛ በሚያውቅ፥ ምስጢራቸውም በማይሰወርበት ሰው። ለምሳሌ አኹን ይኸ በራብ ምክንያት እግዜርን ስለመካድ ነው የተደረሰው?፦

    ‹‹ዘጠኝ ታድናለህ፣ አንድ ትገድላለህ፤
    የሴት ልጅ ነህና፣ ምን ፍርድ ታውቃለኸ።››

Leave a comment