Skip to content

የበጋው መብረቅ ይናገራል

May 22, 2012

በ15 ዓመት ዕድሜው ጠላትን እፋለማለሁ ብሎ የተነሳ፣ ብዙ ተከታዮችን አፍርቶ ጠላት ሊይዝ ሲያሳድደው ሲያሻው ጭልሞ ጫካ ውስጥ ዛፍ ላይ መሰላል ሰርቶ እየተደበቀ፣ ሲያሻው እንደ ምትሃት በጠላት ፊት እየተንጎማለለ ሀገሩን ነፃ ያወጣ ጎረምሳ፡፡

ጃገማ ኬሉ !

የበጋው መብረቅ !

ድንገት ዱብ ባዩ !

ያው የዘር ፖለቲካ ሀገራችን ውስጥ እንደ አስፈሪ ጡር ተመዞ የሚወጋው እየፈለገ ነው፡፡

– ግማሹ “ኢትዮጵያ የፅድቅ ሀገር ነበረች አሁንም ናት” ሲል

– ሌላው “የለም! የለም! የብሄር ብሄረሰቦች አስር ቤት ነበረች አሁን ግን የብሄር ብሄረሰብ ሙዚየምነቷን አረጋግጣለች ይላል፡፡”

– ግማሹ “ኢትዮጵያ ወይም ሞት” ሲል ቀሪው ደግሞ “ወዴት! ወዴት! ጎሳየ ለኔ ህይወቴ” ብሎ ጎሳውን በሃሳብ ይደጉማል፡፡

– “የኢትዮጵያ ታሪክ በመደብ ጭቆና የተሞላ ነው” ሲል ‘ማርክሲስት’ ነኝ ባዩ

– “አይ ! የቅኝ ግዛት ነበር” ይላል ተገንጣዩ – አስንጣዩ (የደረግን ሀረግ ለመዋስ)፡፡

የሆነ ሁኖ ነጭ እና ጥቁር የታሪክ ትርጓሜ ይሄው እንደ ውርስ ሀጢያት አልወርድ ብሎ እሳቱም እየጋመ  ይገኛል፡፡

እነዚህ ሰዎች ያልተገነዘቡት ምን ይሆን? ሲባል መልሱን እንደ ጃገማ ኬሎ አይነት አኩሪ ጀግኖች ናቸው ሊመልሱት የሚችሉት፡፡

ጀነራል ጃገማ   “ነጭ ጤፍ ከጥቁር እንደማይለይ ኢትዮጵያዊያንን ማለያየት አይቻልም!” በሚል ርዕስ በ1986 “ኢትዮጵያዊነት” የተባለ ድርጅት ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ያደረጉት ንግግር፡፡ እነሆ ፡

ከዚህ በመቀጠል በጠላት ዘመን ያየሁትን እና የሰማሁትን ላውጋችሁ፡፡

“ነጭ” ጤፍ ከ “ጥቁር” እንደማይለይ ኢትዮጵያዊያንን ማለያየት አይቻልም!

 

የኢትዮጵዊነት አላማ በኔ አሰተያየት፡-

የኢትዮጵያ አንድነት እና ነፃነት እኩልነት ከተጠበቀ በተፈጥሮ ሃብት የተደላደለች በታሪኳ የነነች ኢትዮጵያ ሳትከፋፈል እና ሳትቆራረስ ለዘላለም እንድትኖር የጎሳ ልዩነት ሳይደረግ በኢትዮጵያ ውስጥ የተወለደ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ኢትዮጵያዊነት ግዴታው እና መብቱም ነው ብየ አምናለሁ፡፡ አንድነት እና ህብረት እንደኛ የአድዋን ድል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ጭምር አስገኝቷል፡፡ ሁለተኛው በአምስቱ የጠላት ዘመን ከየጎሳው ተነሳስተው እና ተውጣጥተው እስከ በመጨረሻ በመጋደል ለነፃነት ያደረሰት አርበኞች ሕያው ምስክሮች ናቸው፡፡

ከዚህ በመቀጠል በጠላት ዘመን ያየሁትን እና የሰማሁትን ላውጋችሁ፡፡

የኢጣሊያ ፋሽስት ሀገራችንን ወርሮ ከለቀቀ 53 ዓመት የሆነ ይመስለኛል፡፡ በዚያን ጊዜ እኔ ልጅ ሁኜ አጎቴ ፊታውራሪ አባዶዩ ዋሚ፣ የሜጫ ባላባት ዘንድ ነበርኩ፡፡ የጠላት ፕላን መጀመሪያ በባላባቶቹ አማካኝነት ህዝቡን እና አገሩን ለማወቅ ባላባተቹን በየአገራቸው ላይ መሾም፣ ሕዝቡን እና አገሩን ከአወቀ በኋላ የህዝቡን አንድት ለማፈራረስ በጎሳ ለመለያየት ጀመረና ኦሮሞዋቹን ከክልላችሁ ውስጥ አማራን ለምን አታስወጡም በማለት ገፈፋቸው፡፡

መሬታችንን ልቀቁ በማለት የጠላት ስልት ያልገባቸው የዋህ ዜጎች እስከመጋደል ከደረሱ በኋላ፣ በአካባቢው የሚገኙ ባላባቶች “ፊትውራሪ አባዶዩን አሳምነን አማራን ከአገራችን ማስወጣት አለብን ወይ?” በማለት ቀጠሮ ጠይቀው አጎቴ ቤት ስብሰባ ይደረጋል፡፡ የስብሰባው አላማ ሳይጀመር የምሳ ሰዓት ደረሰና ምሳ ሊበላ እቤት ልንገባ ስንሄድ ፊትውራሪ አባዶዩ የሰዎቹን አመጣጥ ለምን እንደሆነ ስለሚያውቁ አንድ ኩንታል ሰርገኛ ጤፍ እበራፍ ላይ አስቀምጠው አቆዩዋቸው፡፡

እንግዶቹ ከቤት ሲደርሱ አባዶዩ “ከመግባታችሁ በፊት ይህንን ጤፍ እፈሱ” ይሏቸዋል፡፡ እንግዶቹ ጤፉን ካአፈሱ በኋላ “ነጩን እና ቀዩን” ለዩልኝ ይሏቸዋል፡፡ “አይ ጤፍ ነጭና ቀይ መለየት አይቻልም”፣ ብለው እጃቸውን አራግፈው እቤት ገቡና ምሳ መጋበዝ ጀመሩ፡፡ ምሳ ሲበሉ የፊታውራሪ አባዶዩ ባለቤት አብረው እንግዶቹን ጋብዘው ወጡ፡፡

ከምሳ በኋላ

“እንግዲህ የመጣችሁበት ጉዳይ ገብቶኛል፤ እዚሁ እንነጋገራለን፣ አማራን ከአገራችን ወይም ከክልላችን እናስወጣ፣ አለዚያም እንግደላቸው ለማለት ነው የመጣችሁት አይደለም?” ሲሏቸው

“አዎን ጌታችን ሆይ፤ አንተ የልባችንን ሁሉ ታውቃለህ” ይሏቸዋል፡፡

በዚህ ጊዜ ፊትውራሪ አባዶዩ “ጃገማ” ብለው ይጠሩኝ እና “ልጆቼን ጥራቸው” በማለት ያዙኛል፡፡

ወጣ ብየ ልጆቹን ጠርቸአቼው ልጆቹ ወደቤት ሲገቡ “በሉ ያው አቅርቤላችኋለው እና ልጆቹን ግደሉ ! ከዚሁ እንጀምር !” ብለው ይጠይቃሉ፡፡

እንግዶቹም ደነገጡና “ለምን ልጆቹን እንገድላቸዋለን?” ሲሏቸው ጊዜ “አሁን ምሳ ጋብዛችሁ የወጣችው ባለቤቴ አማራ ነች፤ ቅድም ጤፉን ነጩንና ቀዩን ለይሉኝ ስላችሁ የማይቻል መሆኑን የነገራችሁኝን፤ እኔም ለምሳሌ ነው ያደረግሁት” አሏቸው፡፡ ቀጥለውም :-

“በተለይ በሽዋ አማራና ኦሮሞ ከብዙ ዓመታት ጀምሮ የተጋባና የተቀላቀለ ስለሆነ፤ አሁን በጠላት ግፊት እንዴት ሊለያዩ ይችላሉ ከእናንተ መካከል ከአማራ ጋር የተጋባችሁ እዚህ የላችሁም ወይ?” አሏቸው፡፡

ሁሉም “እኔም ተጋብቻለሁ”፣ “እሱም ተጋብቷል” በማለት ስለተግባቡ ከዚያን ቀን ጅምሮ ግድያው ቆሞ ጠላትም ፕላኑ ተጨናግፎበት አማራው እና ኦሮሞው አንድነቱ ሳይፈርስ ጠላትም አገራችንን ለቅቆ ለመውጣት ተገደደ፡፡ ህዝቡ በዚህ ንጥረ ሀሳብ ሊስማማ የቻለው በፊታውራሪ አባዶዩ የአርቆ ማስተዋል ጭምር ነው፡፡ ከዚህ ከፊታዉራሪ አባዶዩ ዘዴና ምክር በኋላ ነው በአገሩ ላይ የነበረውን አማራና ኦሮሞ ትግሬ ሳይቀር ሁሉም ተስማምተን የአዲስ አለምን ምሽግ ሰብረን ከሰባ (70) በላይ ነጭ ጠላት ገድለን፣ 1500 ጠብመንጃ ማርከን 80 ተዋጊ ዜጎችን ከእስራት ለማስፈታት የቻልነው፡፡

ስለዚህ ከላይ እንዳልኩት አንድነት፣ ነፃነት እና እኩልነት ከተጠበቀ ኢትዮጵያ በጎሳ ሳትከፋፍል ዳር ድንበሯ ሳይደፈርና ሳትቆራረስ በነፃነቷ ትኖራለች ብየ አምናለሁ፡፡

From → Uncategorized

Leave a Comment

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: