Skip to content

መጽሃፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ ኃይሉ

February 19, 2012

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ፕሬስ “ደቂቀ እስጢፋኖስ : በህግ አምላክ”ጌታቸው ሃይሌ (ተርጓሚ) ፣  “መጽሃፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ ኃይሉ ወልደ ታሪክ” ( መንግስቱ ለማ እንደፃፈው)፣  “የነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ ስራዎች” ( መንግስትና የህዝብ አስተዳደር እና አጤ ምኒሊክ  አንድ ላይ፤ በገብረህይወት ባይከዳኝ) ፣“ካየሁት ከማስታውሰው” በልዑል ራስ እምሩ ሃለስላሴ ፣ የብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደ ስላሴ “ወዳጄ ልቤና ሌሎችም “፣የመርስኤ ሀዘን ወልደ ቂርቆስ “የሀያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ፣የዘመን ታሪክ ትዝታየ ካየሁት እና ከሰማሁት 1896-1922” ወዘተ እያሳተመ  እያስደሰተን ይገኛል፡፡

በርግጥ የነጋድራስ የኢኮኖሚ ትንታኔ ካይነስን ይቀድማል ብንልም፣ በርግጥ የእስጢፋኖሳዊያኖቹ ጥንካሬ እና እምነት ቢያስደምመን፣ በርግጥ የነ እራስ እምሩ እና የነየመርስኤ ሀዘንወልደ ቂርቆስ ትዝታ መቶ አመት ወደ ኋላ ወስዶ ቢያሳየንም የአለቃ ለማ ኃይሉ ታሪክ  ግን አስገራሚ እና አስደማሚ፤ ጣፋጭ እና ተወዳጅ ሆኖ አገኝሁት ፡፡

አለቃ ለማ ያልዞሩበት ደብር የለም፣ እውቀትን ፍለጋ ከመቄት እስከ ዋድላ ከዛም ነገላ ሲሉም ደብረታቦር-ዲማ-ደብረ ሊባኖስ- ደብረ ብርሃን- አዲስ አበባ እስከ ሀረር፡፡ ቅኔ ተቀኝተዋል ዘርፈዋልም ያውም የሚነዝር፤ መፅሃፍን እስከ  ሀይማኖተ አበው ድረስ አስተምረዋል፤ የሃይማኖት ክፍፍልን ( ሁለት ልደት ሶስት ልደት ክፍፍል) በቅርብ ያሳዩናል፡፡

ታሪክን እንደ አለቃ አጣፍጦ የሚተርክ ማን ይሆን;

አለቃ እርጅናን:-
እርጅና ብቻህን ና፤

ተከታዮችህ ብዙ ናቸውና፡፡ ብለው አያልፉትም ይልቅስ የሚከተለውን ጣፋጭ ታሪክ ይነግሩናል፡፡

                                                            ☟

             ሰውየው አረጀ፡፡ ቁጭ ብሎ ሳለ፣ ሰውነቱ እጁ እግሩ ይጠያየቁ ጀመር፡፡

‘አይን እንደ ምንድን ነህ ?’ አሉት እጅና እግር፡፡

‘አሄሄ! ሌሊት በጨለማ ምንገዱን ለይቼ እሄድ የነበረ፤ ዛሬ ጠሃይ መለስ ሲል አልታየኝ አለ፡፡’

‘እግር እንደምንድን ነህ?’

‘አየ ! የኔ ነገር ቀርቷል፡፡ አቀበቱን ስወጣ ቁልቁለቱን ስወርድው ስብርስብር እል የነበረ፤ ወንዙን ዘልየ ስሻገር እንደቆቅ እሽከረከር የነበረ፤ ዛሬ የቤቴን መድረኩን መሻገር ተሳነኝ- እወጣ ስል ያሰናክለኛል’ አለ እግር፡፡

‘እጅ እንደምነህ?’

‘አየ! ወንዙን እሻግሬ እመታ የነበረ፤ ወደፊት እወረውራለሁ ያልኩት ወደኋላየ ይወድቅ ጀመረ አለ፡፡’

‘ጥርስ እንደምንነህ?’

‘አየ! ባቄላውን አተሩን ቆሎ ጥሬውን ስበላው ሳደቃቅቀው አጥንቱን የነበረ፤አሁን ፍትፍቱን ለመብላት ተሳነኝ፡፡’

‘ልብሳ እንደምን ሆነሃል አሉት?’

‘ኧኸኸ ! ወትሮ ከነበርኩበት እድር ከፍ ብዬ ወደ አንገት ጠጋ ብዬ ተቀምጫለሁ’ አለ፡፡

‘ሁሉም አባይ ነው አለ ስውየው እውነተኛ ልብ ብቻ ነው! እማረጅ፤ እማይደክም ልብ ብቻ ነው፡፡’

አለቃ የኖሩበት ዘመን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ የሚባለው ጊዜ ውስጥ ነው ከ19ኛው ክፍለ ዘምን አጋማሽ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ባለው መቶ አመት ውስጥ፡፡ ከታላላቆቹ ነገስታት እስከ ተራው ህዝብ ታሪክ የማያውቁት የለም፡፡ ስለ አለቃ ገብረ ሐና እንዲህ ይሉናል፡-

<<አለቃ ገብረሐና- የሞያ መጨረሻቸው እሳቸው አደሉም ወይ? የሐዲስ መምህር ናቸው፤ፍታነገስትን በሳቸው ልክ የሚያውቅ የለም፤ ይኸ የቁጥሩ-መርሐ ዕውሩን አቡሻክሩን ሁሉ የሚያውቅነው፤ ባለሟያ፡፡… አለቃ ገብረ ሐና መችም ለዚህ ለዝማሜ እሚባለው፤ ለመቋሚያ፤እገሌ ይመስለዋል አይባልም፤ከገብረ ሐና ፊት እሚዘም የለም፡፡>>

እያሉ አለቃ የትምባሆ ቅል ይዘው ቤተክርስቲያን እንደገቡና ድንገት ወድቆባቸው እርሳቸውም ( አለቃ) ሊቃውንቱም የገጠማቸውን ድንጋጤ ይነግሩናል አለቃ ለማ፡፡

አለቃ ያላዩት ምን ታሪክ አለ?! በታሪክ “ክፉ ቀን” ስለሚባለው ወቅት እንዲህ ብለው አለቃ ይቀጥላሉ፡-

<<ከብት አለቀና አደለም ረኃብ የሆነው; ከብቱ ያላለቀበት አገር የለ፤ጭርስ ብሎ አገር አለቀ፤ በቆላ ምንምን አልተገኝም፡፡ የኔ አባት እስከ ሶስት መቶ ከብት ነበራቸው፤ አንዲት ጥጃ ተረፈቻቸው አሉ፡፡ ስሟን ‘ሣለሁድረሽ’ አሏት አሉ፡፡

ረኃቡን ያስነሳው የከብቱ ማለቅ ነው፡፡ በምን ይታረስ? መሬት ሳይታረስ እንዲያው እንዳለ ቀረ፡፡ ረሀቡ ያንጊዜውን ከብቱ እንዳለቀ ተከተለ፤ እስከ ሦስትዓመት ድረስ ሰነበተ፡፡

ጅብ ጭርስ አደረገው ሰውን፡፡ አሁን ሥላሴ የተሠራበት ላይ የራስ ደስታ አባት የፊታውራሪ ዳምጠው ቤት ነበረ፣ የምኒልክ የፈረስ ቤት፡፡ እሳቸው ግሸን ተሹመው ሕደዋል፤ ላለቃ ወልደ ያሬድ ተሰጠ ቤቱ፤ እኛም ኸዚያው ኻንድ ቤት ውስጥ ነነ፡፡ ሌሊት ወሰደኝ! ወሰደኝ! ወሰደኝ! ሲል ያድራል፡፡ በበነጋው ማልዳ ጉባዔ ሲሄድ አለቃ ወልደ ያሬድ እንቅልፍ እንደሌለኝ ታውቋል- ለማ ዛሬ ጅብ ስንት ሰው ወሰደ; ይሉኛል፡፡

‘አምስት ስድስት ሰባት ድረስ  ወሰደ  እላለሁ’ በድምጡ በጩኸቱ ‘ይህን ያህሉ ወንድ ይህን ያህሉ ሴት እላለሁ፡፡’ ማ ይወጣል ጅብ ሊከለክል? ሁሉም ደካማ ነው- ረሀብ፡፡ ደሞ እሱን ቢወስደውስ፤ ማን ያድነዋል?

አንዲት ልጅ ወዛ ብላለች- ጋይንት ደስታ እሚባል ነበርና እሱ እየረዳዳት፡፡ ተነስታ ፍሎሃ ወረደች፡፡ ብዙ ሰው የተቀመጠው እዚያ ነው፣ ይኸ ስደተኛው ሁሉ- ተቀበለና እዚያ አረደና በላት፡፡

ልጆቻቸውን ጥቃቅኖቹን እያረዱ የበሉ ሴቶች ብዙ ናቸው፡፡ ሰው ቅጠል በላ፤ ልተበላ ቅጠል የለም፤ ይኸ ቅጠል ቀረ እሚባለውን ነገር አላውቀውም፡፡>>

ከዚህ በላይ ረኃብን ምን ይወክለዋል? ከዚህ በላይ ምን ሀዘን አለ ?!

መቸም የአለቃን መፅኃፍ አለማንበብ ትልቅ ጉዳት መሆኑን መናገር ምርምር አይጠይቅም፡፡ እኔም የኔን ምልከታ ሳጠናቅቅ የአለቃን ታሪክ በቴፕ ቀርፀው በመፅሃፍ አትመው ያቀረቡልንን ታላቁን ባለቅኔ የባለታሪኩ የአለቃ ለማን ልጅ መንግስቱ ለማን እያመሰገንኩ አርሳቸው በመግቢያው የፃፏትን ልብ የምትነካ ነገር አስከትየ ልጨርስ፡፡

 <<አለቃ ለማ ሃይሉ ‘አባቴ አስተማሪየ ‘የሚሏቸው አለቃ ተጠምቆ ትግሬ ናቸው፡፡በቅኔ በብልህ መምህርነታቸው ማዕረግ አክብረው አንከብክበው አለቃ ተጠምቆን የያዟቸው ዲሞች ጎጃሞች ናቸው፡፡ አለቃ ለማን ቤተኛቸው አድርገው ለወይዘሮ አበበች ይልማ የዳሯቸው ጌታ አለቃ ወልደ ያሬድ ሸዬ ናቸው፡፡ አለቃ ለማ ራሳቸው መቄቴ ላስቴ ናቸው፡፡

ይህ የሊቃውንት አባቶቻችን የታላቅነት አርዓያ፤ ባሁኑ ዘመን ትግሬ ነህ ፤ጎንደር ነህ፤ ሐረርጌ ነህ፤ ወለጋ ነህ በመባባልና በማባባል ጊዜና ጉልበታቸውን በከንቱነት የሚያባክኑትን ሁሉ በፅኑ ይወቅሳቸዋል፡፡የታላላቆቹ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸው የመንፈስና የሐሳብ አንድነት ነበር፡፡>>

“አይመቱት ልጅ ሲቆጡት ያለቅሳል” አሉ፡፡ ምነው ዛሬን ባዩ ጋሽ መንግስቱ፡፡

Advertisements

From → My Articles

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: